የወር አበባ ክልከላዎች እና ማኅበራዊ ተጽእኖዎቻቸው፦ በካፋ ዞን ማኅበረሰብ ተተኳሪነት

Authors

  • የኔዓለም አረዶ[1]፣ ደስታ አማረ[2]፣ ደስታ ደሳለኝ[3] እና ፍሬሕይወት ባዩ[4]  

Abstract

 

ይህ ጥናት ከወር አበባ ጋር የተያያዙ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማጥናት ላይ አተኩሯል። ዋና አላማው ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማህበራዊ ተጽእኖ ማሳየት ነው። ጥናቱ በካፋ ዞን በሚገኙ የካፋቾ፣ የናኦ እና የጻራ ብሔረሰቦች ላይ ተወስኗል። መረጃዎች ምልከታና ቃለ መጠይቅን በመጠቀም ተሰብስበዋል። በመረጃ ሰጪነት ወንዶችም ሴቶችም እንዲሁም ለመረጃ ማስተንተኛነት የማህበራዊ ውክልና ንድፈ ሀሳብ ተመርጠዋል። መረጃዎቹ እንደሚያመለክቱት አንዲት ሴት የወር አበባ ስታይ ከቤት ትወጣለች፤ ውሎዋና አዳሯ ከዋናው ቤት ውጪ በተሰራች አነስተኛ መጠለያ ውስጥ ይሆናል፤ እርሷ ያዘጋጀችውን ምግብ ሌላ ሰው አይመገብም፤ በተለይ እርሷ ያዘጋጀችዉን ምግብ ባለቤትዋ ከተመገበ ከባድ ችግር ይከሰታል ተብሎ ይታመናል። የወር አበባ እየታያት እቤት ውስጥ ከገባች ውቃቢ ይጣላታል፤ ልትታወር ትችላለች፤ ልትሞትም ትችላለች የሚል እምነት አለ። በመሆኑም በመኖሪያ ቤትዋ ውስጥ እያለች ድንገት የወር አበባ ቢታያት፣ ከቤትዋ ወጥታ ስትመለስ የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጸምላትና ሁኔታዎችን እንድታመቻች ባህሉ ያስገድዳታል። በጥናቱ ውጤት መሰረት በተጠኑት ብሔረሰቦች ሴትነት በተለይ ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሀጥያት እና ንጹህ ያለመሆን ትዕምርት ተደርጎ ይወሰዳል። አንዲት ሴት የወር አበባ በምታይባቸው ቀናት ከቤተሰብ እንድትነጠል የሚያስገድደው ልማድ በመኖሩም ሴቷ በማኅበራዊም ሆነ በስነልቦና ረገድ የሚደርስባት ተጽእኖ ከፍተኛ ነው። የወር አበባ ለአቅመ ሄዋን የመድረስ መገለጫ ነው፤ ዘር ይቀጥል ዘንድ ተፈጥሮአዊ ጸጋ የሆነው የወር አበባ ሚናም የላቀ ነው፤ በመሆኑም ይህን ማኅበረሰቡ ተረድቶ ሴቶችም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ በቤታቸው እንዲቆዩ አልያም መገለል እንዳይደርስባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በሚመለከታቸው አካላት ቢሰራ መልካም ነው።

 

Downloads

Published

2024-11-05

How to Cite

የኔዓለምአረዶ[1]፣ደስታአማረ[2]፣ደስታደሳለኝ[3]እናፍሬሕይወትባዩ[4] . (2024). የወር አበባ ክልከላዎች እና ማኅበራዊ ተጽእኖዎቻቸው፦ በካፋ ዞን ማኅበረሰብ ተተኳሪነት . ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures), 33(1), 133–156. Retrieved from http://213.55.95.79/index.php/JAELC/article/view/10664